ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለ በዓለ ልደት ቃለ ቡራኬ አስተላለፉ።

0
1 0
Read Time:5 Minute, 12 Second

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ልደትን አስመልክተውየእንኳን አደረሳችሁመልእክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ አንስተው አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅዱስናታቸው ባስተላለፉት መልዕክት ቸርነቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር አምላክ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የተከሠተው ችግር በከፊልም ቢሆን ረገብ ብሎ የሰላም ጭላንጭል እንድናይ አድርጎናልያሉ ሲሆንይህ ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና #ልንወደው #ልናከብረውና #ልንጠብቀው ይገባልብለዋል።

” ሰላም በጠፋ ጊዜ በወገኖቻችን ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ በዓይናችን አይተናል። ” ያሉት ቅዱስነታቸው ” ይህ ዓይነቱ ክሥተት ሊቆም እንጂ ሊቀጥል አይገባም ” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የተገኘው የሰላም ጭላንጭል ወደ ፍጹም አስተማማኝ ደረጃ በሙሉነት እንዲያድግ ሁሉም በኃላፊነት እንዲሰራ በአጽንዖት አደራ ብለዋል።

በተከሠተው አለመግባባት በአጠቃላይ በሕዝብ ላይ የደረሰው ስብራት ከባድ በመሆኑ የዓለም ማኅበረሰብ የተቻለውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ሕዝባችንን እንዲያግዝ  መንግሥትና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የተጀመረውን የሰላም ጉዞ እንዳይቀለበስ በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው ፤ ” ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ልጆቻችን በተለመደው የመተጋገዝ ቅዱስ ባህላችን መሠረት እርስ በርስ #በመረዳዳት ይህንን ፈተና እንድናልፈው በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን ከአደራ ጋር እናስተላልፋለን። ” ብለዋል።

“በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው አመራር የምንገኝ ኃላፊዎች ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማክበር ይጠበቅብናል፤ የሰውን ሕይወት ለመጠበቅ የሰው ሕይወት መጥፋት አለበት የሚል የተሳሳተ አካሄድ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የለውም”
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ይህን የተናገሩት የ2015 ዓ.ም በዓለ ልደትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

° በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
° ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ ፣
° የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፋ የቆማችሁ፣
° በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
° እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ° ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት በሙሉ፣

በዕለተ ልደቱ ሰማያውያንንና ምድራውያንን በአንድነት አገናኝቶ ስለ ሰላም እንዲዘምሩ ያደረገ የሰላም አለቃ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አምስት ዓመተ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

“ወይከውን ሰላም በመዋዕሊሁ፤ በዘመኑም ሰላም ይሆናል” (ዘካ.፱፥፲)

በአበሳው ምክንያት ከፈጣሪው ተለይቶ በሰቆቃ ይኖር የነበረው የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሰላሙ ከተናጋ ብዙ ዘመናትን አስቆጥሮአል፤ የሰላሙ መናጋት የጀመረውም ከእግዚአብሔር ከተለየበት ቀን አንሥቶ ነው፣ መቼም ቢሆን መለያየት ጉዳትን እንጂ ጥቅምን አያስገኝምና ሰው ከእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ከሆነው ሁሉ በመለየቱ ጉዳቱ የበረታ ሆነ፤ ኑሮውም ደፈረሰበት፤ ጣዕመ ሕይወቱም ወደ እሬት ተለወጠበት፤ በዚህም ምክንያት ሰው በጨለማና በሞት ጥላ የተዋጠ ምስኪን ፍጡር ሆኖ ኑሮውን ቀጠለ፤

ይሁን እንጂ ፍቅርና ርኅራኄ ቸርነትና አዘኔታ ምሕረትና ይቅርታ ገንዘቡ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር፣ ሰውን በምሕረትና በይቅርታ ሊቀበለው ወደደ፤ ይህንም በልዩ ልዩ ዓይነተ ነገር ገለፀ፤ እግዚአብሔር የሰው ልጅን መንፈሳዊ ሰላም በእርግጠኝነት እንደሚመልስ ከገለፀባቸው ቃላተ ትንቢት አንዱ “በዘመኑ ሰላም ይሆናል” የሚል ቃለ ሰላም ይገኝበታል፤ የዚህ ቃለ ሰላም መሠረተ ሐሳብ ሲታይ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚሰጠው ዘላቂና ፍጹም ሰላም በመሢሑ በኩል በሚሆነው ቤዛነት እንደሆነ ነው። ከዚህ አኳያ እግዚአብሔር የመሢሑን መምጣት ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጀምሮ ሲገልፅ ቆይቶአል። ዘመኑ ሲደርስም መሢሑ በዚህ ዓለም ተገልፆአል፤ መሢሑ በዚህ ዓለም የተገለፀው በብሥራተ ገብርኤልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰውነትን ተዋሕዶ ነው።

ወልደ እግዚአብሔር በተዋሐደው ሰውነት በቤተ ልሔም ሲወለድ ሠራዊተ መላእክት “ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ ለሰው ልጅ ውድ ነገር የሆነው ሰላም በምድር ላይ ሆነ” በማለት ዘምረዋል። መላእክት በዚህ መዝሙራቸው “የተወለደው ሕፃን ከብዙ ዘመናት በፊት ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም ፤በዘመኑም ሰላም ይሆናል” ተብሎ የተነገረለት የሰላም አለቃ መሆኑን ለዓለም አበሰሩ፤ እረኞችም በተወለደበት ቦታ ተገኝተው የሰላሙን መዝሙር ተካፋይ ሆኑ፤

የጥበብ ሰዎች የሆኑ የምሥራቅ ነገሥታትም አምላክነቱን ለመግለፅ ዕጣንን፣ንጉሥነቱን ለመግለፅ ወርቅን፣አዳኝነቱን ለመግለፅ ከርቤን እጅ መንሻ አድርገው ገበሩለት፤ ለአምላክነቱም ከምድር ወድቀው ሰገዱለት።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!!

እግዚአብሔር ከሰው ጋር ሰላም መፍጠሩን የገለፀው በትንቢት ወይም በምሳሌ ወይም በቃል ብቻ አልነበረም፤ እጅግ በሚያስደንቅ የተዋሕዶ ተግባርም እንጂ፤ በአበሳ ኃጢአት መነሻነት በጠላትነት ተፈርጆ የነበረውን የሰው ልጅ መውደዱ ብቻ ሳይሆን፣ ጭራሽ ሰውነቱን ሰውነት አድርጎ ወይም አካሉን አካል አድርጎ መገለጡ፣ የሰላሙ ጥልቀትና ምጥቀት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው፤ የሰማይ ሠራዊትም “የሰው ልጅን እጅግ ወደደው” በማለት በከፍተኛ አድናቆት የዘመሩለት የሰውን ሰውነት ተዋሕዶና የራሱን አካል አድርጎ በመንበረ ጸባኦት እንዲቀመጥ አድርጎት በማየታቸው ነው፤

ይህ የዕርቀ ሰላም ውጤት ነው፤ ዕርቀ ሰላም የማይፈታው ችግር እንደሌለ ይህ አምላካዊ ዕርቅ ግዙፍ ማስረጃ ነው፤ እግዚአብሔር ሰውን የታረቀው በምሕረትና በይቅርታ ብቻ አይደለም፤ ወይም ላቅ ያለ ቁሳዊ ስጦታ በመስጠትም አይደለም፤እግዚአብሔር ሰውን የታረቀው “ሰው በመሆን” ነው፤ በዚህ ምሥጢረ ተዋሕዶ እግዚአብሔር ሰው ሲሆን ሰውም እግዚአብሔርን የመሆን ዕድል በማግኘቱ በውጤቱ ሰው በተዋሕዶተ ቃል በመንበረ ጸባኦት ተቀምጦ ሰማያውያን መላእክትን ጨምሮ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሊሆን ችሎአል።
ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ክብረ ወስብሐተ ከለልኮ፤ ወሤምኮ ውስተ ኲሉ ግብረ እደዊከ፤ ወኲሎ አግረርከ ሎቱ ታሕተ እገሪሁ፤ የክብርና የምስጋና ዘውድን ጫንህለት፤ በእጆችህም ስራ ላይ ሾምኸው፤ሁሉንም ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፤ እርሱ መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” ይላል ፤

በመሆኑም የተወለደው ሕፃን በዘመኑ ዘላቂና ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ ሰላምን ያስገኘ ብቻ ሳይሆን በተዋሕዶተ ቃል በመንበረ ጸባኦት ተቀምጦ የመላእክትና የፍጥረት ሁሉ ገዥ ስለሆነ ከምንም ሁሉ በላይ መሆኑን እናስተውላለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

እግዚአብሔር እጅግ የሚወደን መሆኑን የምናውቀው እኛን መስሎ ሳይሆን እኛን ሆኖ በመካከላችን በመገኘቱ ነው፤ ታዲያ እግዚአብሔር እኛን ይህን ያህል ከቀረበንና ከወደደን እኛም በዚሁ መጠን ልንዋደድ አይገባንምን? እንድናደርገውና እንድንፈጽመው የሰጠን አደራስ ለሰው ሁሉ እንዲህ ያለ ፍቅር እንዲኖረን አልነበረምን? ሰዎች በየትም እንኑር በየት እርስ በርስ በመፈቃቀርና በመዋደድ በሰላም የመኖር አምላካዊ ግዴታ እንዳለብንስ ዘነጋነውን? በሰላምና በፍቅር የመኖር ጉዳይ ለሰዎች እንደመብት ሳይሆን እንደ ግዴታ ነው፤ ምክንያቱም የነገርየው ውስጠ ይዘት የመኖርና ያለመኖር አንድምታ አለውና ነው፤

እግዚአብሔር በሕይወት እንድንኖር እኛን ፈጥሮአል፤ ይህ የእግዚአብሔር ቀዋሚ ፈቃዱ ነው ፤በመሆኑም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማክበር ለሰው ልጆች ሁሉ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ኃላፊነት አለብን፤ ይልቁኑም በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው አመራር የምንገኝ ኃላፊዎች ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማክበር ይጠበቅብናል፤ የሰውን ሕይወት ለመጠበቅ የሰው ሕይወት መጥፋት አለበት የሚል የተሳሳተ አካሄድ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የለውም፤

ምክንያቱም በአንድ በኩል እያጠፉ በሌላ በኩል እጠብቃለሁ የሚል አካሄድ ከኪሣራና ከጥፋት ነጻ አያደርግምና ነው፤ በዚህ ስሑት አስተሳሰብ ዓለም በሽቅድምድም እያመረተችው ያለው የፍጥረተ እግዚአብሔር ማጥፊያ መሣሪያ ከአጥፊነት በቀር የአልሚነት ሚና አለው ብሎ መናገር ፈጽሞ አይቻልም፤

በዚህ አጥፊ መሣሪያ የእግዚአብሔር ፈቃድ ተጥሶ ሕፃናትና እናቶች፣ ዓቅመ ደካሞችና አረጋውያን በሕይወት የመኖር ዕድል አጥተዋል። ይሁንና ቸርነቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር አምላክ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የተከሠተው ችግር በከፊልም ቢሆን ረገብ ብሎ የሰላም ጭላንጭል እንድናይ አድርጎናል፤ ይህ ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና ልንወደው ልናከብረውና ልንጠብቀው ይገባል።

ሰላም በጠፋ ጊዜ በወገኖቻችን ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ በዓይናችን አይተናል። ይህ ዓይነቱ ክሥተት ሊቆም እንጂ ሊቀጥል አይገባም። ስለዚህ የተገኘው የሰላም ጭላንጭል ወደ ፍጹም አስተማማኝ ደረጃ በሙሉነት እንዲያድግ ሁላችንም በኃላፊነት እንድንሠራ በዚህ አጋጣሚ በአጽንዖት አደራ እንላለን።

በመጨረሻም
በተከሠተው አለመግባባት በአጠቃላይ በሕዝባችን ላይ የደረሰው ስብራት ከባድ በመሆኑ የዓለም ማኅበረ ሰብ የተቻለውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ሕዝባችንን እንዲያግዝ፣ መንግሥታችንና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችም የተጀመረውን የሰላም ጉዞ እንዳይቀለበስ በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲሠሩ፣ ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ልጆቻችንም በተለመደው የመተጋገዝ ቅዱስ ባህላችን መሠረት እርስ በርስ በመረዳዳት ይህንን ፈተና እንድናልፈው በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን ከአደራ ጋር እናስተላልፋለን።

መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *