የማርኮ ሩቢኦና የጎንደር አደባባዮች ግልጽ መልእክት፣ በአፋብን ታጣቂዎች ላይ የሕግና የዲፕሎማሲ አደጋዎች
የማርኮ ሩቢኦና የጎንደር አደባባዮች ግልጽ መልእክት፣ በአፋብን ታጣቂዎች ላይ የሕግና የዲፕሎማሲ አደጋዎች፣
በዶ/ር ሶስና ታደሰ (የፖለቲካና ስትራቴጂክ ጥናት ክፍል)
ከትግል ሞራል ወዴት?
መግቢያ፦ የሞራል ልዕልና መሸርሸር እና የትረካዎች ፍጭት
በኢትዮጽያ ውስጥ የአማራ ሕዝብ በደረሰበት የዘር መድሎና ጭፍጨፋን ለመመከት የጀመረው የሕልውናና የፍትሕ ተጋድሎ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዋና መታወቂያው፣ ሕዝባዊ ቅቡልነቱና የዓለም አቀፍ ድጋፍ ማግኛ መሠረቱ «የሞራል ልዕልና» (Moral High Ground) ነበር። ይህ ትግል የሕዝብን ሕልውና የማስከበር፣ ታሪካዊ አጽመ-ርስትን የማስመለስና የማስከበር፣ ፍትሐዊት ሀገር የመገንባት ታላቅ ዓላማ ያነገበ እንጂ፤ የሕዝብ ሀብትና የሲቪል ተቋማትን የማደምደቅ አውዳሚ የሽብር መስመር አልነበረም።
በቅርቡ በጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም (October 17, 2026) ጥዋት በጎንደር፣ በወሎና በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች የተካሄዱትን ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ በሁለት አጽራረ-ትረካዎች (Counter-narratives) መካከል ፍጭት ሲደረግ ይስተዋላል። በአንድ በኩል የብልጽግና አገዛዝ የካድሬ መዋቅሩንና አምባገነናዊ ግፊቱን ተጠቅሞ እንቅስቃሴውን «የብልፅግናና የቀይ ባሕር አጀንዳ ድጋፍ» አስመስሎ ለዲፕሎማሲ ጥቅም ለመሸጥ ሲራወጭ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ራሱን «አፋብህን» ብሎ የሚጠራው ስብስብና የፅምዶ አራጋቢዎቹ በተለያየ የሶሻል ሚዲያ እና በዓለም አቀፍ ድልድዮች በኩል ሕዝቡን «በግዳጅ የተሰበሰበ የፖለቲካ ሰለባ» አድርገው በመሳል የራሳቸውን የከሰረ የፖለቲካ ውድቀት ለመሸፈን ይሞክራሉ።
ነገር ግን በመሬት ላይ ያለውን ታሪካዊ፣ ወታደራዊና የመልከዓ-ምድር ፖለቲካ (Geopolitical) እውነታ በአፅኖት የሚመረምር አካል የሚደርስበት ድምዳሜ ግልጽ ነው፦ ይህ አጋጣሚ የአገዛዙ ድጋፍ ሳይሆን፣ ከሕወሓትና ከቀጣናዊ ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የአማራን የህልውና ትግል አሳልፈው በሸጡት የ«ፅምዶ aka ትብብር» ደላሎች ላይ የተቃጣ የቀጥታ ሕዝባዊ ቁጣ፣ ማግለልና የስህተት ዋጋ ነው!
ሕዝብ የራሱ የሆነ የአስተውሎት እና የትዝብት ማሕደር አለው፤ በተለይ የአማራ ሕዝብ የአማራ ፋኖን ትግል በቅርበት ሲከታተልና ሲታዘብ ወደ ትግሉ ሲቀርብና ሲርቅ ማስተዋላችን ያለፉት የ3 ዓመት ተኩል ታሪካችን ነው። ሕዝቡ በእውነት ይህንን ሰልፍ ለማድረግ ያስገደደው የብልፅግና ሥርዓት ተመችቶት ሳይሆን፣ ያመናቸው ልጆቹ ስለከዱት የመጣ ቁጣ መሆኑን በጥልቀት መመርመር ግድ ይለናል። በተለይም በጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም (October 17, 2026) ጥዋት ላይ በጎንደርና በወሎ አደባባዮች ላይላዩን ሲታይ የብልፅግና የድጋፍ የሚመስል እውነታው ግን በፅምዶ ደላሎች ላይ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ቁጣና ማግለል ከተከናወነ ከሰዓታት በኋላ፤ በዚያው ዕለት ምሽት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢኦ በአዲስ አበባ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት የተገንጣይ ሐይሎች ‘የሽብር ድርጊት’ ሲሉ መኮነናቸው፤ የሕዝቡ አስተውሎትና ቁጣ ከዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ አቅጣጫ ጋር የተጣጣመና ቅደመ-ግንዛቤና ቅድመ-አስታውሎት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል።
1. የካይሮው ድብቅ ስብሰባና የ10ሺህ ፋኖ ጥያቄ ሴራ
በቀጣናው የተዘረጋውን አደገኛ የመልከዓ-ምድር ፖለቲካዊ ወጥመድ ነጥቦቹን በማያያዝ ስንመረምረው የሚከተሉት ጥብቅ ስትራቴጂካዊ እውነታዎች ይገለጣሉ፦
1. የ10ሺህ አማራ ፋኖ ተዋጊዎች ጥያቄ (Instrumentalization)፦ ሕወሓት «ፅምዶ/ትብብር» በተባለው መዋቅር አማካኝነት ቢያንስ 10,000 የአማራ ፋኖ ወጣት ተዋጊ እንዲቀርብለት ለበላይ አካላቱ (ለግብፅና ኤርትራ) ጥያቄ ማቅረቡና ጥያቄው ወደ አፋብህን መውረዱ ይገመታል። በራሱ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያጣውና የሰው ኃይል እጥረት ያጋጠመው ሕወሓት፣ የአማራን ወጣት በ«ትብብር» ስም ለራሱ የፖለቲካ ህዳሴና ወልቃይት/ራያን የመያዝ አጀንዳው «ቅጥረኛ ወታደር» (Proxy Agent) አድርጎ ለመጠቀም አቅዷል።
2. አማራን የጦር አውደ-ግንባር (Battleground) የማድረግ ሴራ፦ በግብፅ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ሶማሊያ መሪዎች ደረጃ የተካሄዱት ድብቅ ውይይቶችና ስትራቴጂካዊ ውሳኔዎች ዋና ዓላማ፣ ጦርነቱን ተገፍቶ ወደ አማራ ክልል እንዲገባ ማድረግ ነው። የቀጠናው ኃይሎች «የአማራን ሕዝብ በዚህ ጦርነት ማውደም ከተቻለ፣ ዳግም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ማንሰራራት አትችልም» የሚል ስትራቴጂያዊ ግምገማ በማስቀመጥ አማራን የውክልና ጦርነት ማገዶ ለማድረግ አቅደዋል።
3. መሠረተ-ልማቶችን የመደምሰስ አጀንዳ፦ ጦርነቱ በክልሉ ውስጥ ሲፋፋም ሕዝቡ እንዲፈናቀል፣ ትልልቅ ድልድዮች፣ የኤሌክትሪክ ስቴሽኖች እና ዋና ዋና የሲቪል መሠረተ-ልማቶች እንዲወድሙና ሕዝቡ ለውጭ ኃይሎች ጥገኛ እንዲሆን መታቀዱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
2. የሞራል ልዕልና መሸርሸር፦ ከ«ሴቶች ረሽነናል» እስከ «የሲቪል አውሮፕላን ድብደባ»
የፅምዶ ደላሎች በሕዝቡ ዘንድ የተተፉበት ምክንያት በመሬት ላይ በፈጸሙት የክህደት ቁማር ብቻ ሳይሆን፣ በከባድ የሞራል፣ የዲፕሎማሲና የሰብአዊ መብት ውድቀታቸው ጭምር ነው፦
ቀደም ሲል የአፋብን ቃል አቀባይ የሆነው አስረስ ማረ በጥር 2018 (Jan 3, 2026) ለዓለም አቀፉ ሚዲያ (BBC አማርኛ) ወጥቶ «ሴቶችን ረሽነናል» በማለት የፈጸመው ያልበሰለ፣ የሕግ ግንዛቤ የጎደለውና የትግሉን ሞራላዊ ማማ ያወረደ ከባድ የፖለቲካ ስህተት ስናስታውስ፤ በመቀጠል ደግሞ በ«ፅምዶ» መረብ ውስጥ ባሉ የአፋብንና የፅምዶ የሶሻል ሚዲያ አራጋቢዎች በጥቅምት 2026 (October 1, 2026 በTikTok Live) በተናገሩት የሽብር ፕሮፖጋንዳ «የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ (Boeing) አውሮፕላን አየር ላይ ተመቶ ይውደቅ» የሚለው ጥሪ የዚያው የአስረስ ማሬ የከሰረና አደገኛ መንገድ ቀጥተኛ ተቀፅላ መሆኑን ያሳያል! እንደገና ባሳለፍነው ሳምንት የሕወሓት ጥበቃ ልምና፦ አስረስ ማሬ የሕወሓት ፕሮፖጋንዲስት በሆነው ሪዕዮት ሚዲያ በመቅረብ «የሕወሓት (TPLF) አመራር እንዳይፈርስ የትግራይ ወጣቶች ሕወሓትን ይታደጉ» ብሎ ሲለማመጥ መደመጡ፣ አፋብን ድርጅቱ በአማራ ስም የተቋቋመ «የአማርኛ ተናጋሪ ወያኔዎች» መሆኑን አረጋግጧል።
የእነዚህ 3ቱ እንደምሳሌ የተጠቀሱ አደገኛ ንግግሮች ብቻ መዋቅራዊና በሕዝብ ስነ-ልቦናዊ ትስስር ብሎም በትግሉ ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ የከፋ መሆኑን በግል ያሳያሉ፦
● የሕግና የሞራል ውል ማጣት፦ አስረስ ማሬ በወቅቱ የፈጸመው ተራ የቃላት ስህተት አይደለም፣ ግልጽ ወንጀል ነው! የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ሕግን (IHL) የሚጥስ እንደነበር ሁሉ፤ ዛሬም በቲክቶክ «ቦይንግ አውሮፕላን አየር ላይ ይመታ» የሚለው ጥሪ በ1971ዱ የሞንትሪያል ስምምነትና በ1944ቱ የቺካጎ ስምምነት (Article 3 bis) መሠረት ፍጹም «የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ሽብርተኝነት» (Incitement to Aviation Terrorism) የሚያስደምድም ከባድ ወንጀል ነው።
● የሲቪል አቪዬሽን ላይ ያጣጣረ የጋራ የሽብር ጥሪ፦ በትግራይ ክልል ይፋዊ ደብዳቤ ላይ «በሲቪል አቪዬሽንና በበረራዎች ላይ እገዳ እንዲደረግ» ከተላለፈው ጥሪ ጋር በተቆራኘ መልኩ፣ የፅምዶ አራጋቢዎች በቲክቶክ «የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን ይመታ…» እያሉ የሽብር ጥሪ በማስተላለፍ የሀገር ሀብትንና የሲቪል ተቋማትን ለመደመሰስ ያቀዱት ሴራ ይፋ ሆኗል።
● ለብልፅግና አገዛዝ የሚሰጥ የፕሮፓጋንዳ ካርድ፦ አገዛዙ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መድረክ «ተቃዋሚዎቼና ፋኖዎች የሕግ የበላይነት አፍራሾችና የሽብርተኞች ስብስብ ናቸው» የሚለውን የሐሰት ትረካ ለማስረገጥ ሲታገል ነበር። የአስረስ ማረ ዓይኑን ያፈጠጠ የወንጀል መግለጫ እና የቅርቡ የቦይንግ አውሮፕላን የይመታ ጥሪ ለአገዛዙ ይህንኑ የሐሰት ካርድ በእጁ አሳልፈው የሰጡ የከሰሩ መንገዶች ናቸው!
3. የአማራ ፋኖ ይህንን የሽብር ቅስቀሳ በጊዜ ካልመከተ የሚገጥመው መዋቅራዊና ዓለም አቀፋዊ የሕግ አደጋዎች
የአማራ ፋኖ ‘አፋብን’ ወይም ‘ትብብር’ በሚል መረብ ውስጥ በስሙ የሚደረገውን የሲቪል ተቋማት የመደምሰስና የሽብር ቅስቀሳ፣ ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖሩበት፣ በርካታ አለምአቀፍ የዲፕሎማቲክ ተቋማት በሚገኙበት ትልልቅ ከተምች ላይ የሚፈፀም የድሮን ሆነ የቦንብ ጥቃት በይፋ ሰብሮ ካላወገዘና ራሱን ካላጠራ፣ በዓለም አቀፍ ሕግና የፖለቲካ ሳይንስ መርሆዎች መሠረት የሚከተሉት ከባድ አደጋዎች ይደቅኑበታል፦
1. በዓለም አቀፍ ደረጃ በ«ሽብርተኝነት» የመፈረጅ አደጋ (Terrorist Designation)፦ በዓለም አቀፍ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግጋት (UN Security Council Resolutions) መሠረት፣ የሲቪል አቪዬሽን ጥቃት ማስፈራሪያዎችን በዝምታ ማለፍ ወይም ይሁንታ መስጠት አንድን የታጠቀ ሐይል ከ«ነፃነት ታጋይነት» (Freedom Fighters) ቀይሮ ወደ «ሕገ-ወጥ የሽብር ቡድን» (Violent Non-State Actor / Terrorist Entity) ደረጃ ይከተዋል። ይህ ከተከሰተ ደግሞ የፋኖ እንቅስቃሴ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ በዓለም አቀፍ አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) እና በምዕራባውያን ሀገራት ዘንድ በይፋ ታግዶ ሕጋዊ ቅቡልነቱን ያጣል።
2. የዲያስፖራውና የገንዘብ እንቅስቃሴ መታገድ (Financial & Assets Sanctions)፦ የሽብርተኝነት ቅስቀሳን በጊዜ አለመመከት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ደጋፊዎችን፣ የፋኖ አስተባባሪዎችንና የገንዘብ አሰባሳቢዎችን አደጋ ላይ ይጥላል። የፋትፍ (FATF) እና የዓለም አቀፍ ባንክ ሕጎች በሽብርተኝነት ጥሪ ከተጠረጠሩ አካላት ጋር የሚደረግን ማንኛውንም የገንዘብ ዝውውር ስለሚያስቆሙ፣ የዲያስፖራው የፋይናንስና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ይዘጋል።
3. የመሪዎች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መጠየቅ (Universal Jurisdiction & Command Responsibility)፦ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕግ መሠረት «የዕዝ ኃላፊነት» (Command Responsibility) የሚባል መርህ አለ። የፋኖ መሪዎች በስማቸው የሚደረገውን የሲቪል አውሮፕላን የይመታ ጥሪ በይፋ ካላወገዙ፣ ወደፊት በሚፈጸም ማንኛውም ጥፋት በዓለም አቀፍ ሕግ «የሽብር ድርጊት አጋሪና ተባባሪ» (Complicity in Terrorism) ተደርገው በዓለም አቀፍ የእስር ትዕዛዝ ሊፈለጉ ይችላሉ።
4. የሕዝባዊና የፖለቲካ ቅቡልነት ማጣት (Loss of Domestic Legitimacy)፦ የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታገለው የሕግ የበላይነትና ፍትሕ እንዲሰፍን እንጂ ሀገራዊ የጋራ ሀብት የሆነው የሲቪል ተቋማት እንዲወድሙ አይደለም። እንዲህ ያሉ ጥሪዎችን አለመመከት የሕዝቡን አመኔታ የሚያሳጣና ትግሉን የብልፅግና አገዛዝ ለሚያካሂደው በእነሱ አጠራር «የሕግ ማስከበር» ትረካ ተጋላጭ ያደርገዋል።
4. የታሪክ ቁስል፣ የፋኖዎች መከዳት እና የሕዝቡ አስተዋይነት
የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ሲጀመር፣ የሸዋ፣ ጎንደር፣ የወሎና የጎጃም ፋኖዎችና ሕዝቡ የያዙት መሠረታዊ አቋም የፀና ነበር፦ «ከሕልውናና ከርዕዮተ-ዓለም ገዳዮቻችን ከሕወሓትና ከኦነግ ጋር አንሰራም፣ ብልፅግና ጋርም አንደራደርም፤ የሕዝባችንን የፍትህ ጥያቄና አጽመ-ርስትና ደም ለፖለቲካ ቁማር አናውልም!» የሚል ፅኑ አቋም እንደነበራቸው ይታወቃል፤
ይሁንጂ በተለይም ከአፋጎ አመራሮች የነበረው የፖለቲካ ብልሽት አካሄድ ስር ሰዶ በአንድነት ስም አፋብን የሚል ድርጅት ከመሰረቱ በኋላ፣ ከአማራ ሕዝብ የዘወትር ጠላቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር ትግሉን በድለላ አሳልፈው ለቀጠናው ቁማር ሽጠውታል፣ እነ ዘመነ ካሴና አስረስ ማረ በአፋብህን ስም ከሕወሓት ጋር ጥምረት ሲፈጥሩ፣ የመጀመሪያዎቹ ተከጅዎችና ሰለባዎች ከርዕዮተ-ዓለም ገዳዮች ጋር አንደራደርም ያሉ የጎንደር ፋኖዎች ነበሩ። ይህ የክህደት መንገድ የጀመረው ቀደም ብሎ እንደሆነ ግን ከዚህ ላይ ልብ ማለት ግድ ይላል። አፋብህን/ፅምዶ የሕወሓትን የ50 ዓመት መዋቅራዊ የዘር ማጥፋት፣ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የራያ ወረራ «እንደ ተራ የቀደመ የታሪክ ቅሬታ» አቅልሎ በማቅረብ፣ የአማራን ሕዝብ የሕልውና፣ የክብርና የዕጣ-ፈንታ ጉዳይ ለሕወሓትና ለውጭ ኃይሎች የውክልና ጦርነት «ማገዶ» ለማድረግ የሄደበት መንገድ በታሪክ ፊት ትልቅ ክህደት ሆኖ ተመዝግቧል።
እዚህ ላይ በግልጽ ሊሰመርበት የሚገባው ዋናው ነጥብ፦ የፅምዶን ደላሎች በስራቸው ማጋለጥ ሆነ መውቀስ ወይም የአማራ ፋኖን የትግል ጉዞ ብልሽት ማረም በጭራሽ የብፅግና አገዛዝን መደገፍ አይደለም! ሕዝቡ ይህ አገዛዝ ብቻ ሳይሆን ይህንን ስርዓት ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሊታገሉት የሚገባ አጥፊ ሥርዓት መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል።
ነገር ግን የፅምዶ ደላሎችና የፖለቲካ ደናቁርት ስብስቦች በፈጠሩት ክህደት፣ ትርምስና የትግል ግርዶሽ ምክንያት፣ ሕዝቡ ሙሉ አቅሙን በአገዛዙ ላይ እንዳያሳርፍ እንቅፋት ሆነዋል። አገዛዙ የወሎ፣ የጎንደርም ሆነ የመላው አማራ ወዳጅ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። ዛሬም እንደትናንቱ የሕዝቡ ብቸኛ ወዳጁ የራሱ አንድነታዊ አቅም፣ የራሱ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጥንካሬ ብቻ ነው! ከዚህ አገዛዝ ሰላምና ፍትሕ መጠበቅ መጨረሻው መጠፋፋት በመሆኑ፤ ሕዝቡ ከፊቱ የተደቀኑ ሁለቱንም አደጋዎች የሚያከሽፍበትን መንገድ «ድርብ መከላከል» መርህ ለመከተል የሰከነ ምልከታ ማድረግ ይኖርበታል።
● አገዛዙን መመከት፦ በአማራ ሕዝብ ላይ የተደቀነውን መንግስታዊ ጥቃትና አምባገነንነት በራሱ ሉዓላዊና ገለልተኛ የመከላከል አቅምና መዋቅር ይመክታል፣ ይህንን ለማድረግ ከወዲሁ ከጠላት የፀዳ አማራዊ አደረጃጀትን የመመስረትና የማፅናት ሀላፊነት አለበት።
● ደላሎችንና ቅጥረኞችን መከልከል፦ የሕዝቡን ፍትሐዊ ትግል ለሕወሓትና ለውጭ ኃይሎች የውክልና ጦርነት አጀንዳ አሳልፈው የሸጡትን የ«ፅምዶ/አፋብህን» ደላሎች በይፋ መቃወሙን እየገለፀ ይገኛል። ይህ የሚያሳዬው ቢያንስ አማራ በሚለው የወል ስሙ ከዚህ በላይ እንዲነገድበት አለመፍቀዱን ነው።
6. «ሕዝብ Dynamic ነው!» — እውነተኛው ፋኖ ሊወስደው የሚገባው አስቸኳይ እርምጃ
ሕዝብ ወይም ማህበረሰብ የማይቀየር ግዑዝ ሳይሆን፤ እንደ ሁኔታው፣ እንደ መረጃውና እንደ ድርጊቱ አስተሳሰቡን፣ አቋሙንና አሰላለፉን በየጊዜው የሚቀይር፣ የሚማርና የሚወስን ሕያው አካል ነው»። «ሕዝብ Dynamic ነው!» ሕዝብና ታጋዩ ወጣት በፖለቲከኞች ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ደላሎች እንደፈለጉ የሚነዱ «ዕውር ተከታይ» (Blind Follower) አይደሉም! ሕዝብ የራሱ የሆነ የትግል መቁጠሪያ ካላንደር አለው፣ ብዙ የፖለቲካ መሪዎች፣ የፓርቲ ካድሬዎች ወይም የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች (Influencers) ሕዝብን እንደፈለጉ የሚነዱት፣ ያመነውን ነገር ሁሉ አምኖ የሚቀበልና የያዘውን አቋም የማይቀይር «የዋህና ተከታይ» አድርገው ያስባሉ። ነገር ግን «ሕዝብ Dynamic ነው» ሲባል ሕዝብ የራሱ የሆነ የአስተውሎት፣ የትዝብትና የመመዘኛ ሚዛን አለው ማለት ነው። ዛሬ አንድን ኃይል ወይም መሪ ደግፎ አደባባይ ስለወጣ ብቻ ነገም ቢሆን ያንን አካል ይደግፋል ማለት አይደለም። ሕዝቡ በስሜት አይነዳም፤ የአንድ አካልን ስህተት ሲያይ ወደ ሌላኛው አረመኔያዊ አገዛዝ አቅፍ ውስጥ አይገባም። ይልቁንም ሁለቱንም አደጋዎች (የአገዛዙን አምባገነንነት እና የደላሎችን የሽብር/የቅጥረኝነት አጀንዳ) እኩል በመገምገም የራሱን ገለልተኛና ሉዓላዊ አቅም የመገንባት ጥበብን በሐይል ሚዛን ይተገብራል።
በመሆንም በዚህ ሰአት ግራ በመጋባት ገለልተኛ መሆን አይቻልም ቢያንስ ለሕዝብ የሚቆረቆሩና ለሕዝባቸው ክብር ያላቸው የአማራ ፋኖዎች ያጡትን ሕዝባዊ ድጋፍ መልሰው ለማግኘት ቢከብዳቸው እንኳን በቅኔ ብልፅግናን በመደገፍ የተነሳባቸውን ሕዝባዊ የተቃርኖ ቁጣ ማብረድ ግድ ይላቸዋል በመሆኑም በ«ፅምዶ» መረብ ውስጥ ያልገቡ እውነተኛ የፋኖ አካላት፣ መሪዎችና ታጋዮች የሚከተለውን አስቸኳይና አንገብጋቢ እርምጃ መውሰድ አለባቸው፦
1. የሽብርተኝነት እንቅስቃሴንና የሽብር ፕሮፖጋንዳን በይፋ ማወገዝ፦ በስማችሁና በትግላችሁ ስም በማህበራዊ ሚዲያ በፅምዶ ዲጅታል ሰራዊት በደላሎች የሚደረጉ የሲቪል ተቋማትና የሕዝብ ሀብት የማውደም የሽብር ጥሪዎችን «የእኛን ፍትሐዊ ትግል አይወክሉም» በማለት በጥብቅ መግለጫ በይፋ አውግዙ!
2. የትግሉን የሞራል ልዕልና ማስከበር፦ ትግላችሁ የተበደለውን ሕዝብና የሀገር ሀብት የማዳን እንጂ የሀገር ሀብት የማድቀቅና የሽብርተኝነት እንዳልሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለሕዝባችሁ በግልጽ አስታውቁ።
3. «የድርብ መከላከል» (Double Defense) መስመርን መያዝ፦ አማራ በራሱ ፍትሐዊ መርህ፣ በጥብቅ ድርጅታዊ ዲሲፕሊንና በማዕከላዊ ዕዝ ሥር በመደራጀት ሁለቱንም አደጋዎች (የብልፅግናን አገዛዝ እና በትብብር ስም የፅምዶ ደላሎችን የውድመት/የሽብር አጀንዳ) እኩል የመመከት የጸና አቋም ያዙ!
ማጠቃለያ
የአማራ ሕዝብ ትግል እንደ ወንዝ ነው — ቆሻሻውን፣ የጠላት ቅጥረኞችን፣ የ«ፅምዶ» ደላሎችን፣ በስሙ የሚነግዱ ባንዳዎችን ሁሉንም ወደ ዳር ገፍትሮ ጥሎ፥ ትክክለኛ የአማራ መሰረታዊ ጥያቄዎችን አነግቦና ንጹሁን የነፃነት መስመር ይዞ ይጓዛል!
ዛሬ በወሎና በጎንደር የተስተዋለው ሕዝባዊ ቁጣና ማግለል በሌሎች የአማራ ከተሞችና በሌሎች ክልሎች እንደሚስፋፋ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ይህ አጋጣሚ ለፅምዶ ደላሎች የተቃጣ የማይቀረው የስህተት ዋጋ ነው! ሕዝቡ ይዞት የሚወጣው የባነር መልዕክት ብልፅግና ለመደግፍ ሳይሆን የአፋብንን ክህደት ጉዞ ለመበቀል የተደረገ ቅኔያዊ ሰልፍ መሆኑን መረዳት ግድ ይላል።
በየጫካውና በየቀጠናው ያላችሁ እውነተኛ የፋኖ አርበኞች ሆይ፣ በስማችሁ ከሚደለቀው የሽብር ፕሮፖጋንዳ፣ የከሰረ መንገድና በስማችሁ የሚነገደውን የቀጠናው ሽብር ንግድ በቁጣ ሰብራችሁ በመውጣት፣ የትግላችሁን ሞራላዊና ሕጋዊ አሸናፊነት በፅናት አስክበሩ!
ድል ለአማራ ሕዝብ!
ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
