phonto
0 0
Read Time:8 Minute, 6 Second




የኢትዮጵያ ምሁራን ከወዴት አላችሁ…? — ክፍል ፩

ዘ ኢትዮጵያን ትሪቢዩን

የኢትዮጵያ ምሁራን ከወዴት አላችሁ…?

ክፍል ፩

በሙሉዓለም ገ/መድኀን


የዝግጅት ክፍሉ መቅድም

የአደባባይ ድርቅ

አገር በህልውና አደጋ አፋፍ ላይ ስትቆም ቀድማ የምትጠራው ጦር ሠራዊቷን አይደለም፤ ሕሊናዋን ነው። በታሪክ ውስጥ የኅብረተሰብ ሕሊና ተሸካሚ ተብሎ የተሰየመው ደግሞ ምሁሩ ነው። ስለሆነም ሙሉዓለም ገ/መድኀን ‹‹የኢትዮጵያ ምሁራን ከወዴት አላችሁ?›› ሲል የሚያሰማው ጥሪ የግል ብሶት ሳይሆን የዘመኑ የህልውና ጥያቄ ነው።

ይህ ጥሪ የሚደርሰን በተለየ ወቅት ላይ ሆነን ነው። አገዛዙ ከምርጫው ማግስት ፍጹም የፓርላማ የበላይነት ጨብጦ፣ ‹‹ሀገራዊ ምክክር›› የተባለው ሂደት አስፈጻሚ ፕሬዚደንትነትን ወደሚያሰፍን የሥልጣን ማዕከላዊነት ሲያዘነብል፣ የ‹‹መደመር›› ትርክት አገሪቱ የተዘፈቀችበትን ቀውስ ‹‹አስደናቂ የለውጥ ጉዞ›› አስመስሎ ሲያቀርብ — ዝምታ የቅንጦት ሳይሆን የተባባሪነት ማኅተም በሆነበት ሰዓት ነው ይህ መጣጥፍ የሚነበበው።

ጸሐፊው የአገሪቱን ምሁራን በሦስት ጎራ ይመድባቸዋል፦ በዝምታና በምንግዴለሽነት የተጠመዱት፣ ‹‹የአዕምሮ ዝሙት›› (Intellectual Prostitution) ፈጻሚዎቹ፣ እና እንደ ዋልያ ለዘር የተረፉት የአደባባይ ምሁራን። ሙግቱን ለማጽናት ከጋናዊው ኢኮኖሚስት ጆርጅ አይቴ እስከ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ መሳይ ከበደ፣ ከዣን ፖል ሳርትር እስከ ኖም ቾምስኪ ያሉ ድምጾችን ያሰልፋል። የሁሉም ማጠንጠኛ አንድ ነው፦ ግፍ በሚፈጸምበት ሰዓት ‹‹ገለልተኛ ነኝ›› ማለት፣ በራሱ ከአጥፊው ጎራ መሰለፍ ነው።

‹‹ግፍ በሚፈጸምበት ሰዓት ‘ገለልተኛ ነኝ’ ማለት፣ በራሱ ከአጥፊው ጎራ መሰለፍ ነው።››

ትሪቢዩን ይህን ጽሑፍ ለአንባቢው የሚያቀርበው ለዚሁ የሞራል ጥያቄ ስለሚወግን ነው። የምሁሩ ሚና፣ የፕሬስ ነጻነትና የተጠያቂነት ጉዳይ የዝግጅት ክፍላችን የጀርባ አጥንት ናቸው።

ሆኖም መጣጥፉ ምሕረት የለሽ ነው። ስም በስም ይጠራል፤ ትናንት በተቃውሟቸው ይደነቁ የነበሩትንም አይራራም። በአማራው ሕዝብ ላይ የደረሰውን መጠነ ሰፊ በደል ‹‹ሕግ የማስከበር ዘመቻ›› በሚል የሚሸፍነውን ትርክትም ይገፍፋል። እነዚህ ውንጀላዎች ከባድ ናቸው፤ ስለሆነም እንደ ወትሮው ሁሉ ትሪቢዩን ገጾቹን ለመልስ፣ ለማስተባበያና ለክርክር ክፍት አድርጎ ያቀርባል፤ የተጠቀሱት ስሞችም ሆኑ አካላት የማብራሪያ መብት አላቸው።

ይህ የጽሑፉ የመጀመሪያ ክፍል ነው፤ ሙግቱ በሁለተኛው ክፍል ይቀጥላል። ጥያቄው ግን ገጹን ገልጦ ወደ አነበበው አንባቢ ተመልሶ ይመጣል፦ ዝምታን የመረጥን ሁላችን፣ ‹‹ከወዴት አለን?››

— የዝግጅት ክፍል · ዘ ኢትዮጵያን ትሪቢዩን

§

የምሁራን ክህደት፡ ከዝምታ እና ምንግዴለሽነት እስከ የአዕምሮ ዝሙት (Intellectual Prostitution) — በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ውስጥ ሰፊ ምርምር የሚጠይቅ ሀሳብ ነው።

ኢትዮጵያ ህመም ከዳተኛ ምሁራን እና ካድሬ እንደሆኑ ካለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ምስቅልቅል አገራዊ ታሪካችን ያየነው እውነታ ነው። ዓለም በመለወጥ ሂደት ላይ ነች፡፡ የለውጥ ሕግጋት ተፈጥሯዊ ዑደት ቢኖራቸውም የለውጥን አስገዳጅነት የግድ እንዲሆን የሚያደርጉት ተሳታፊዎቹ ናቸው፡፡

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን የለውጥ ፍጥነት ብንመለከት እንኳ፣ የጸረ-ቅኝ ግዛት ትግሎች ለፍሬ ሲበቁ፣ ሀገራት ልዖላዊነትን ሲተዋወቁ፣ የሰብዓዊና የዲሞክራሲ መብቶች ተቋማዊ ቅርጽ መያዝ ሲጀምሩ… የሌጋሲው ባለቤቶች ምሁራን ነበሩ። በእነዚህ መስኮች የምሁራን ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡

የአፍሪካ ጸረ-ቅኝ ግዛት ተጋሎ ላይ ምሁራን የነበራቸው ሚና ሳይዘነጋ፣ ከነጻነት በኋላ በነበሩ ነጻ-መንግሥታትን የማቆም ሂደት ውስጥ አብዛኞቹ ምሁራን ከሕዝባዊነት ይልቅ ጥቀመኝነት እያየለባቸው አህጉሪቷን የግፍ ምንጭ አድርገዋታል፡፡

በምክር ሰጭነታቸውና በምንግዴለሽ ዝምታቸው የለውጥን ተፈጥሯዊ ሂደት ቀሰስተኛ እንዲሆን ከማድረግ በዘለለ የለውጥ ዕድሎችንም አምክነዋል፡፡

ድኀረ-ቅኝ ግዛት በአፍሪካ ለታዩ የርስ በርስ ጦርነቶች፣ የነቀዙ ሥርዓታት ላደረሷቸው ግፍና መከራዎች አያሌ የአፍሪካ ምሁራን ሚና አላቸው፡፡ በአንጻሩ ከቅኝ ግዛት ወዲህ ባሉ ግዜያት በአፍሪካ ያሉ ምሁራን የማህበራዊ ለውጥ ዐውድ ሚናቸው በእጅጉ አጠያያቂ ነው፡፡

ይህን ሃሳብ ከሚሞግቱት ጸሐፍት አንዱ ጋናዊው ኢኮኖሚስት ጆርጅ አይቴ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ አይቴ “We Let Africa Down Badly” የሚል ርዕስ በሰጠው መጣጥፉ ላይ አፍሪካውያን ምሁራን ላይ በከረሩ ቃላት ቅሬታውን ይገልጻል፡፡

የአፍሪካ ምሁራን ከበዝባዥ መንግሥታት ጋር በመተባበር አስነዋሪ ተግባር ፈጸመዋል የሚለው አይቴ፣ ‹‹የፖለቲካ ሰዎች፤ የበቁ መምህራን፤ ጠበቆች እና ሃኪሞች እራሳቸውን እንደሴተኛ አዳሪ በችሎታ ከነሱ አናሳ የሆኑትን ወታደራዊ ወሮበሎችን ፈላጭ ቆራጮችን ለማገልገል ራሳቸውን አቅርበዋል። ደግመው ደጋግመው መልሰው መላልሰው እየተደፈሩ፤ ክብራቸው እየተገፈፈ፤ እየተሰደቡ፤ ተሰልፈው ካገለገሉ በኋላ እንደቆሻሻ ጥራጊ ይጣላሉ … የባሰም ሊሆን ይችላል። እነዚህኞቹ ሲጠረጉና ሲጣሉ፤ የበለጠ ክህሎት ያላቸው ምሁራን ሴተኛ አዳሪዎች በቦታቸው ለመተካት አንዱ በአንዱ ላይ በመጨፈላለቅ ይሽቀዳደማሉ›› ሲል የአህጉሪቱን ምሁራን ነውረኝነት ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት ገልጾልናል፡፡

በጆርጅ አይቴ ምሁራዊ ግሳጼ የደረሰባቸው ምሁራንን በግብር የሚወክሉ፣ ፊደል የቆጠሩ አሽከሮችን ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ታሪኳ ደጋግማ አስተናግዳለች፡፡ ከሃምሳ ዓመት ወዲህ ባለው ሀገራዊ ጉዟችን ውስጥ በቂ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ፕ/ር መሳይ ከበደ ለዚህ ሙግት ዋቢ የሚሆን መጣጥፍ አለው፡፡ “Beyond Ideology: The Betrayed Task of Ethiopian Intellectuals” በሚል ርዕስ መሳይ፣ የኢትዮጵያ ምሁራንን ገቢራዊ ማንነት በተጠየቅ ሞግቷል፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ መበደልና በፍትሕ አልባ ሥርዓት ውስጥ መሰቃየት ምሁራን የሚያሳዩት ደንታ ቢስነት ሳያንስ ለአምባገነናዊው መንግሥት የየብሔራቸውን ጥግ ይዘው በመቆም የሚሰጡት ድጋፍ እጅግ አሳዛኝ ተግባር መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ዛሬ የደረስንበት ሁኔታ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ግድየለሽና አድርባይ ብቻ ሳይሆኑ ንጉሠ ነገሥታዊው ሥርዓት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ አምባገነንነት በጥልቀት እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኃላፊነት ወይም ተጠያቂነት ያለባቸው መርዘኛና ሥር ነቀል የሆኑ ምሁራንን አፍርታለች፡፡››

የሚለው መሳይ፤ አውቶክራሲያዊ የነበረው ንጉሠ ነገሥታዊው ሥርዓት በጣም አደገኛና ይበልጥ አፍራሽ በሆነ አምባገነናዊ አገዛዝ እንደተተካ በጽሁፉ ላይ ይሞግታል፡፡

ዛሬ የዐቢይ አህመድ ከዳሚ ሆኖ የተገኘው ፕ/ር ዓለማየሁ ገ/ማርያም በተመሳሳይ ተጠየቅ “Ethiopia: The Irresponsibility of the Privileged?” በሚለው ቀደም ያለ ጽሑፉ፣ የኢትዮጵያ ምሁራንን ኃላፊነታቸውን የዘነጉ ግድ የለሽ ስለመሆናቸው ሞግቶ ነበር።

ይህ ሰው ዛሬ ዋናው የዐቢይ አህመድ ከዳሚ ነው። “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” በሚለው የወረራ ጉባዔ ላይም ተሳታፊ ነው። ለማመን የሚከብደው ነገር የሸዋ አማራ ነው።

የኢትዮጵያ ምሁራን የሞራል ግዴታቸውን በመርሳት፤ የግል ደስታቸውን ከማሳደድ ባሻገር፤ ለራስ ለማትረፍ ከመሯሯጥ ባለፈ፤ በፕሮግራም ታስሮና ተለጉሞ ከዚያ ውጪ የማይንቀሳቀሱ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቅ ግኡዝ ሮቦት ሆነዋል። አገር እየፈረሰች ምሁራን በከፍተኛ ምንግዴለሽነት በዝምታ ተቀምጠዋል።

በየትኛውም ሀገር ያሉ ምሁራን የማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና የሳይንሳዊ ለውጥ ግንባር ቀደም ኃላፊ መሆን እንዳለባቸው አጠያያቂ አይደለም። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ የሚመስለው ምሁራኑ ከሚያሳዩት ባህሪ የተነሳ ነው።

የአገሪቱ ምሁራን በሦስት ጎራ ሊታዩ ይችላል፦

ዝምተኞች ወይንም ምንግዴለሽነት፣

የአዕምሮ ዝሙት (Intellectual Prostitution) ፈፃሚዎች እና

የአደባባይ ምሁራን (እንደ ዋልያ ለዘር የተረፉ)

ባህሪያቱን ለማስቀመጥ ያህል እንጅ፣ እያንዳንዱን ምድብ እዚህ ላይ ለመተንተን ጊዜና ሁኔታዎች አይፈቅዱም። የሆነው ሆኖ፣ አሁን ባለው ሁኔታ የአደባባይ ምሁራን ተመናምነው አደባባዩ ላይ ለሥልጣን እውነትን የሚናገሩ ሰዎች በመጥፋት ላይ ናቸው።

የዚህ ሥረ-ነገር ከደርግ የቀይ ሽብር ሰቆቃ የሚነሱ ድርብርብ የምሁራን ፍርሃት ወለድ በሽታዎች ቢኖሩም በዐቢይ አህመዱ ዘመን የሚታየው ዝምታ፣ ምንግዴለሽ እና አዕምሯዊ ዝሙት ያልተለመደ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ውስጥ ሰፊ ምርምር የሚጠይቅ ሀሳብ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለች ተፈራራቂ አምባገነናዊ ሥርዓታት ስታስተናግድ በኖረች ሀገር የምሁራን ሚና ማህበረ-ፖለቲካዊ ለውጥ ላይ ቢያተኩር ይመረጥ ነበር። ኢኮኖሚውስ ከተባለ… የማህበራዊ ኀይሎች ንቃተ ህሊናቸው በነሆለለበት ሁኔታ የፖለቲካ ነጻነት ተሟጋችና አምራች ኀይል መገንባት የማይታሰብ ነው።

ይህን መንገድ የመረጡ፣ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በእጅጉ ያሳሰባቸው የትናንትም ሆነ የዛሬ ቄሳራውያን የሴራ ፖለቲካን በተጠየቃዊ አጀንዳዎች የሞገቱ፣ ከአካዳሚያዊ የልሂቅነት ክፍተቶችን ከመድፈን ጎን ለጎን አገዛዙ ያነበረውን ብሔራዊ ድንዛዜ በመግፈፍ የአደባባይ ምክንያተኝነትና የሃሳብ ልዕልና ዜጎች እንዲያገኙ የታገሉ ጥቂትም ቢሆኑ የአደባባይ ምሁራን ነበሩን! ዛሬ ግን አደባባዩ ላይ በመጥፋት ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ በአደባባይ ምሁራን ድርቅ የተመታች አገር ሆናለች።

‹‹ኢትዮጵያ በአደባባይ ምሁራን ድርቅ የተመታች አገር ሆናለች።››

መናኛ ጥራዝ ነጠቆች ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር መጫወቻ እያደረጓት ጥቂት የማይባሉ ምሁራን ከ፯ኛ ክፍል በላይ መደበኛ ትምህርት ባልዘለቀ ሰው እየተመሩ የአዕምሮ ዝሙትን መርጠዋል።

ጥቅመኝነት ቤቷ የት ነው ቢባል የዐቢይ አህመድ ከዳሚ ሆነው በተሰለፉ ምሁራን ፊት ፈልጓት።

መሃይምነትን ታገለ የሚባለው ደርግ ከምሁራን አያያዝ ሌጋሲው አኳያ ፀረ ዕውቀት ነበር፤ ወያኔ ምሁራንን የሚያሳድድ የአድርባዮች ቤት ነበር። ዐቢይ አህመድ ደግሞ የምሁራንን የአዕምሮ ዝሙት ያስፋፋ፣ ምሁር አምካኝ ነው!

በጥቅሉ ጉዳዩ ጥናት ቢፈልግም፣ አሁን ባለሁ ሁኔታ የዘንድሮ ምሁር አንድም ምንግዴለሽ ነው፤ አልያም ለሥልጣን እውነትን ከመናገር ይልቅ ፥ በሥልጣን ያደረ የአዕምሮ ዝሙት ላይ ነው የሚታየው። በዝምታ አልያም በሚና የአገር አፍራሾቹ አጋዥ ካልሆነም የገዥው ኃይል ሥልጣን አስቀጣይነት የኢትዮጵያ ምሁራን መገለጫ ሆኗል።

በርግጥም የኢትዮጵያ አንዱ ደዌ ከዳተኛ ምሁራን ውርሳቸው መቀጠሉ ነው። ይህ ደዌ ማርከሻ መድኀኒት እስካልተገኘለት ድረስ ኢትዮጵያ ከአዙሪቱ መውጣት አይቻላትም!

በየትኛውም አገር ታሪካዊ የለውጥ እና የህልውና አደጋ ማዕበል ውስጥ፣ ምሁራን የኅብረተሰቡ የሞራል ማንጸሪያ፣ የነጻ አስተሳሰብ ምንጭ እና የሕዝብ ድምፅ ሆነው እንዲያገለግሉ ይጠበቃል።

ይኹን እንጂ ዛሬ ኢትዮጵያ ባለችበት ኹለገብ እና አገረ-መንግሥቱ ህልውናው እየተፈተነ ባለበት ፖለቲካዊ አዙሪት ውስጥ፣ የምሁራኑ ድምጽ መክሰሙ ብቻ ሳይሆን፣ ህልውናዊ ሚናቸውም ጭምር ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ፣ የምሁራኑ ገጽታ በኹለት ጠርዘኛ መገለጫዎች የተተበተበ ነው፤ ይኸውም አጥፊ በሆነ ዝምታ እና ምንግዴለሽነት የተጆበነው ገለልተኝነት እና በሌላ በኩል ራስን ለሥልጣን እና ለጥቅም አሳልፎ በመስጠት የሚታየው ለአገዛዝ ማደር ነው።

ይኽ እውነታ በፖለቲካ ማኅበረሰባዊ ሳይንስ እና በፈላስፋዎች ዘንድ ከሚታወቀው ‹‹የአዕምሮ ዝሙት›› ኃልዮት በኩል ሲፈከር፣ የአገሪቱን ቀውስ ይበልጥ ውስብስብ እና ተስፋ የለሽ ያደርገዋል።

በመከራ ወቅት ውስጥ እያለፈ ያለ አገር፣ የምሁሩን አዕምሯዊ ኃይል መያዝ ሲገባው፣ ‹‹ገለልተኛ ነኝ›› በሚል ሽፋን የሚመርጠው ዝምታ፣ ከገለልተኝነትም በላይ ትልቅ የሞራል ሞት እና የሰብዓዊነት መንጠፍ ነው።

በፈረንሳዊው ፈላስፋ ዣን ፖል ሳርትር እና ዛሬም አልጋ በያዘው ቾምስኪ መሰል አሰላሳዮች ዘንድ እንደተበየነው፣ ምሁር ማለት ማኅበራዊ ኃላፊነት ያለበት ብቻም ሳይሆን የዚያ ማኅበረሰብ ሕሊና ጭምር ነው።

ግፍ ሲፈጸም፣ አገር ስትበታተን እና ሕዝብ ሲሰቃይ፣ ‹‹እኔ ከፖለቲካ ነጻ ነኝ›› ማለት፣ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ምርጫ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹ከአውዳሚነት ጋር ማበር›› ማለት ነው። በአሁናዊ ምሳሌ ‹‹እኔ ከፖለቲካ ነጻ ነኝ›› ማለት፣ ከኦሕዴድ አገር አፍራሽነት ጎን መሰለፍ እንደማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ አውድ፣ ብዙዎቹ ምሁራን ከግል ደኅንነት ፍርሃት፣ ከሥራ ዋስትና ማጣት እና ከ‹‹እኔ ምን አገባኝ›› ከሚል ፍጹም ግለኛ አስተሳሰብ በመነሳት ዝምታን መርጠዋል። ይኽ ዓይነቱ ምንግዴለሽነትም፣ በአገዛዙ በኩል የሚፈጸሙ ስህተቶችን እና የፖሊሲ ውድቀቶችን በዝምታ ማጽደቅ በመሆኑ፣ ለአገሪቱ መፍረስ ቀጥተኛ ተባባሪ አድርጓቸዋል።

ምሁሩ ዝም ሲል፣ ሕዝብ መንገድ የሚጠቁመውም ማጣቱም ሆነ፣ የሚነፍገው እና የሚታለለውን ይረዳው ዘንድ በቀን ጭለማ ውስጥ መውደቁ በትውልዶች ውድቀት የተጻፈ የሐዘን ትውስታ ነው።

ዛሬ ለከብት እረኝነት የማይበቁ በዕድሜ የበሰሉ በዕውቀት በደቀቁ ሰዎች የግራ ቀኝ ፖለቲካው ኢትዮጵያን ወደ ገደል ጫፍ እየገፏት ምሁራኑ፣ ሕዝብና አገር የሚድኑበትን አቅጣጫ ከማሳየት ይልቅ ጥጋቸውን ይዘው ይታያሉ፡፡

ከዝምታው ባሻገር፣ ሌላኛው አደገኛ ገጽታ ደግሞ የተወሰኑ ‹‹ምሁራን›› ከጊዜው የሥልጣን ባለቤቶች ጋር ያላቸው አንሶላ ተጋፋፊነት ነው።

‹‹የአዕምሮ ዝሙት›› የሚተሰኘው ጽንሰ-ሐሳብ የሚያተኩረው፣ አዕምሯዊ ዕውቀትን፣ የምርምር ነፃነትን እና የሞራል ልዕልናን ለግል ጥቅም፣ ለገንዘብ፣ ለሹመት ወይም ለአገዛዝ አሳልፎ በመስጠት ላይ ነው።

ይኽ ኃልዮት እንደሚያብራራው፣ የአዕምሮ ዝሙት ከዋኞች እውነትን እያወቁ በሥልጣን ጥማት አልያም በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተነሳስተው ሐሰትን እንደ እውነት ይለብጣሉ፤ የገዥዎችን ወንጀል በ‹‹ሳይንሳዊ›› ሽፋን ያጥባሉ።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ክስተትም፣ ከዚኽ ኃልዮታዊ ጭብጥ ሌላ ምን ሊያብራራው ይችላል?

ለሥልጣን እና ለሆድ ሲባል ሐቅን ማዛባት፣ አገሪቱ በገባችበት የኢኮኖሚ፣ የሰላም እና የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ ሕዝቡ በመከራ ውስጥ እያለ፣ እነዚህ ግለሰቦች የአገዛዙን ‹‹አስደናቂ የለውጥ ጉዞ›› እያስመሰሉ ምሁራዊ ማዕቀፍ ለመደገፍ ራሳቸውን ‘ለዐራት ኪሎ ገበታ’ አቅርበዋል።

የዕውቀት ባለቤቶች መሆን የነበረባቸው ‹‹ምሁራን››፣ የመደመርን ትርኪምርኪን መዳኛ መንገድ ሊያደርጉ አፈር ሲልሱ ከማየታችን ባለፈ፣ የአገዛዙን የፖለቲካ ትርክት ያለሂስ እና ያለመተቸት በመቀበል፣ ለገዥው አካል የፕሮፓጋንዳ ማስተጋቢያ በመሆን እየገረዱት ነው።

ለምሳሌ በአማራ ሕዝብ ላይ የታወጀውን የዘር ማጥፋት ዓላማ ያለው ጦርነት ‹‹ሕግ የማስከበር ዘመቻ›› የሚል ማብራሪያ ሲሰጡ ይታያል፡፡ የጦር ወንጀል ድርጊቶችን ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ ስኬቶች›› የሚል ‹‹ትንታኔ›› ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ የአማራው ሞት ‹‹ሕጋዊ መሠረት›› እንዲይዝ የሚደረገው በእነዚህ የአዕምሮ ዝሙት ፈፃሚ ምሁራን ‹‹ትንታኔ/አስተያየት›› በኩል ነው።

እውነተኛ ምሁር ለሕዝብ እንጂ ለሥልጣን ወንበር አያጎነብስም ቢባልም፣ ዛሬ የሚታየው እውነታ፣ ምሁራኑ የዕውቀት ነፃነታቸውን ለተላላኪነት በመሸጣቸው የሕዝብን መታመን ብቻም ሳይሆን፣ ራሳቸውን የሰብዓዊነት መንጠፍ ህያው ማስተማሪያ አድርገውታል።

የምሁራን ዝምታ እና የአዕምሮ ዝሙት በአገር ህልውና ላይ የሚያስከትሉት አውዳሚ ውጤት ሁለገብ እና ጥልቅ ነው።


…ይቀጥላል — ክፍል ፪

© ዘ ኢትዮጵያን ትሪቢዩን · መጣጥፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ የተጠቀሱት ግለሰቦችና አካላት የማብራሪያና የመልስ መብት አላቸው።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *